Unsere Geschichte

የቤተ ክርስቲያን አመስራረቱ

በፍራንክፈርት ከተማ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን በወንጌል ለመድረስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ራዕይ በተቀበሉ የእግዚአብሔር ሰዎች አነሳሣሽነት ሚያዝያ 13 ቀን 1990 ዓ.ም. (የስቅለት ቀን) ሰባት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአንድ መኖሪያ ቤት የጸሎት ፕሮግራም ጀመሩ።

በዚህ በተጠቀሰው ቀን የተገኙት ክርስቲያኖች በየሳምንቱ በመገናኘት ቃሉን ለማጥናትና በጸሎትም ለመትጋት ውሳኔ አስተላለፉ። ባጭር ጊዜ ውስጥ የተካፋዮች ቁጥር በፍጥነት ስላደገና በመኖሪያ ቤትም በነጻነት ፕሮግራም ማካሄድ ስለከበደ ከነሐሴ/መስከረም 1990 ዓ.ም. ጀምሮ ፕሮግራማቸውን በአንድ የጀርመኖች ቤተ ክርስቲያን (Freie Christengemeinde Frankfurt) በማድረግ ከመኖሪያ ቤት ወጥተው በቤተ ክርስቲያን መሰብሰብ ጀመሩ።

በዚህ ወቅት የማይረሳ ነገር ቢኖር በሚያስገርም ሁኔታና ፍጥነት የብዙ ነፍሳት መዳን ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በፍራንክፈርትና አካባቢው የሚኖሩ ከአገር ቤት የመጡ አማኞች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ስለተጨመሩልንና በእግዚአብሔርም ሥራ አብረውን ስለተጠመዱ ተጨማሪ ብርታትና ጉልበት ሆነውናል።